Warning: Undefined array key "access" in /home2/negadras/public_html/ethioreaders/articles/index.php on line 1
“ስለ ክርስቲያን ሥነ-ምግባር መሠረት”

ዋና ገጽ | ጦማር
+ - Font Size  
 
 

“ስለ ክርስቲያን ሥነ-ምግባር መሠረት”

  


ያ ሰው ሞተ አሉኝ፣ እንዴት ያ ሰው ይሙት?
በሕይወት ሲያስተምር፣ ለሰው ልጆች ሕይወት፣
ተቀበረ አሉኝ፣ ከቶ እንዴት ይቀበር፣
ሙት ሕያው እንዲሆን፣ በቁሙ ሲያስተምር!

“ስለ ክርስቲያን ሥነ-ምግባር መሠረት” ብፁዓን ንጹሓነ ልብ፤ ገጽ 165

ከወራት በፊት “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” ዘየአውዱት ከመ ዳመና”ን ባወጣሁ ጊዜ እንደገለጽኩት፣ “የዶ/ር እጓለ ባለቤት ከባሕር ማዶ መጥተው፣ “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” የተባለውን መጽሐፍ በድጋሚ በአርቲስቲክ ማተሚያ ቤት እያሳተሙት መሆኑንና በቅርቡ እንደሚወጣም ጓደኛቸው ዶ/ር ምክረሥላሴ አበሰሩኝ ስል ጽፌ ነበር። በተጨማሪም፣ ደራሲው የአባታቸውን፣ የአለቃ ገብረ ዮሐንስ ተሰማንም ታሪክና ስራዎች የሚዘክር መጽሐፍም አዘጋጅተው ስላለፉ፣ እርሱም ጭምር ከላይ በተጠቀሰው ማተሚያ ቤት እየታተመ እንዳለና መገባደጃውም ላይ እንደሆነ” ዶ/ር ምክረሥላሴን በመጥቀስ ጽፌ እንደነበረ የሚታወስ ነው።

ይኼው የዶ/ር እጓለ ገብረዮሐንስ ሁለተኛ መጽሐፍ፣ “ስለ ክርስቲያን ሥነ-ምግባር መሠረት” ብፁዓን ንጹሓነ ልብ፣ አዲስ አበባ በ1983 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ታተመ። ይህም እትም በ1983 ዓ.ም የተባለው መጽሐፉ ለሕትመት ዝግጁ የነበረበትን ጊዜ ለማውሳት ነው። ደራሲው መጋቢት 23 ቀን 1983 ዓ.ም በናይሮቢ ኬንያ ከማረፋቸው ቀደም ብሎ የተዘጋጀ ስለሆነ ነው። ይኼው መጽሐፉ ለአቅመ-ሕትመት ከደረሰ ከ21 ዓመታት በኋላ ከአንባቢያን እጅ ደረሰ ማለት ነው። ዋጋው ኪስ አይጎዳም። ያንን የሚያህል ቁምነገረኛ መጽሐፍ በ30.00 የኢትዮጵያ ብር ገዝቶ ቁምነገር መዝረፍ ያጓጓል። ገጽ በገጽ ሲገልጡት ከ እሰከም ስለሌለው ሃሴትን በእጅጉ ያጭራል። ይህም መጽሐፍ እንደ ቀዳሚው/ታላቅ ወንድሙ “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ”፣ በአዳዲስ ሃተታ የታጨቀ መጽሐፍ ነው። ይኼኛውም የተለየ ጥልቀት አለው። ደጋግሞ ማንበብ የበለጠ መጠቀም ነው። ባጠቃላይ፣ ውብ ነው! ድንቅ ነው! ... ምናልባትም፣ በአንድ ክፍል ብቻ መገምገም በቂ ላይሆን ይችላል። እንዲያውም “ንፉግነት ነው!” ሊባል ይችላል።

ያም ሆኖ፣ አሁንም የምንገመግመው መጽሐፍ እጅግ ከፍ ያለ የዋጋ ድልድል የሚሰጠው፤ የፍልስፍና፣ የሃይማኖት የሥነ-መለኮት፣ የታሪክ፣ የትምህርት፣ የቋንቋና የማህበራዊ ሳይንስ ይዘት ያለው ስራ ነው። እንደሚታወቀው፣ በሀገራችን ፍልስፍና-ነክነት ያላቸው መጽሐፍት ቁጥር እጅግ በጣም አናሳ ነው። ይህም የሆነው በሁለት ምክንያቶች ነው።

አንደኛ፣ ሀገሪቱ ከሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አንስቶ ከውጭው ዓለም፣ በተለይም የግሪክና የሮም ሥልጣኔዎች ከለማበት አካባቢ ጋር ሙሉለሙሉ ስለተቆራረጠችና፣ የብቸኝነት ኑሮዋን ስለቀጠለች፤ ለፍልስፍናና ለምርምር የተዘረጋ ወንበርና የቆመም ትምህርት ቤት ስለታጣ ነው። በዋናነት የምንኩስና መስፋፋትና የመካከለኛው ዘመን Middle Age በመላው ዓለም መግባት ነው። ትምህርት ወይም ዕውቀት የሚባለው ነገር ሕሊና በገዛ ራሱ ሕግጋት እየተመራ በመመራመር የሚገኝ መሆኑ ቀርቶ አንዲት መጣፍ በመተርጎም የሚገኝ ሆነ። የክርስትና ትምህርት የማናቸውም ነገር መጨረሻ መደምደሚያ ሆነ።

ሁለተኛውም ምክንያት ከአንደኛው የሚወጣ ነው። በምስራቁና በምእራቡ መካከል በተጧጧፈው የመስቀል ጦርነት Crusade የተነሳ፣ ኢትዮጵያም በሯን ከውስጥ እንድትቀረቅር ተገዳ ነበር። ታዋቂው የእንግሊዝ ታሪክ ጸሐፊ፣ ኤድዋርድ ጊበን እንዳለው፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ አራት መቶው የፖርቹጋል ወታደሮች መምጣት ድረስ፣ “ኢትዮጵያ ዓለምን ረሳች፤ ዓለምም ኢትዮጵያን በተራው ረሳት!”

እርግጥ ነው ከመካከለኛው ዘመን መግባት በፊት፣ በጥንት ዘመን ኢትዮጵያውያን የትምህርት፣ የንግድና የወታደራዊ ግንኙነቶች ከግሪክና ከመካከለኛው ምስራቅ ጋር ስለነበራቸው፣ የፍልስፍናና የሃይማኖትም መጽሐፍቱም ቢሆኑ ለኢትዮጵያውያን አዲስ አልነበሩም። ዶ/ር እጓለ እንደገለጹት፣ “ኢትዮጵያውያን ከሌሎች የአፍሪካ ሕዝቦች ከሚለዩበት ምክንያቶች ዋናው፣ ከእስራኤላውያን ቀጥለው አምስቱን መጽሐፈ ሙሴን የራሳቸው አድርገው ሲመሩበት በመኖራቸው ነው፤” ስለ ክርስቲያን ሥነ-ምግባር መሠረት፣ ገጽ 70። በዚህም ሳይወሰን፣ የጽላተ-ሙሴን፣ በአክሱም ፂዮን ለዘመናት የራሳቸው ያደረጉ ብቸኛ ሕዝቦች እንደሆኑ ይታመናል። የሥነ ምግባርና የፈሪሃ እግዚአብሔርን መርኾዎች በልባቸው ጽላት የጻፉ አማኒያን ሕዝቦች መሆናቸውም እሙን ነው።
ወደዋናው ትኩረታችን እንመልስ። ... “ስለ ክርስቲያን ሥነ-ምግባር መሠረት ብፁዓን ንጹሓነ ልብ”፣ መጽሐፍ ደራሲ ዋናው የትምህርት ጥናታቸው ፍልስፍናና ሥነ-መለኮት በመሆኑ፣ የመጽሐፋቸው ይዘት ምንም ያህል አያስደንቅም። ፍልስፍናን ሕሊናንና ሃይማኖትን ለማስታረቅም ያደረጉት ጥረት የሚደነቅ ነው። “ሃይማኖት ጸረ-ሕሊና ወይም ህየንተ ሕሊና ሆኖ የሚቆይ ነገር አይደለም። መልዕልተ ሕሊና ነው እንጂ። ግንኙነታቸው የላይና የታች ነው። የሕሊና ላዕላይ ደረጃ ሃይማኖት ይባላል፤” ገጽ፣ 50። ነገር ግን፣ መጽሐፋቸው በኢትዮጵያ የሥነ-ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፈራንና የተለየ ቦታን የያዘ ለመሆኑ ጥርጥር የለኝም። እኔ እስከማውቀው ድረስ፣ በይዘቱ እስካሁንም ድረስ ተወዳዳሪ የለውም። ከላይ እንደገለፅኩት፣ መጽሐፉ በፍልስፍና፣ በሥነ-መለኮት፣ በታሪክ፣ በትምህርትና በቋንቋ የሚሰጠው ፋይዳ የላቀ ነው። ማለትም፣ ቃላት የሚፈለጉበትን ዘይቤና ሃሳብ በዕምቅ ጥልቀት እንዲገልጡ ሆነው ተደክሞባቸዋል።

በገጽ 18 እና 19 ላይ እንደገለጹት ሁሉ፣ የክርስቲያናዊ ሥነ-ምግባር መሠረቱ ያለው በ“አንቀጸ ብፁዓን” ወይም በተራራው ስብከት ላይ ነው። ያም ስብከት፣ እንደ ደራሲው አባባል ከሆነ፣ “የሰው ልጅ ለዳግም ልደት፣ ለዘላቂ ተሐድሶ እድል እና ችሎታ ያገኘበት ትምህርት ነው።” ካሉ በኋላ፣ የመጽሐፋቸው ዓላማም፣ “ለክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን የሌላ ሃይማኖት ተከታዮችንና የነፃ አስተሳሰብ ሰዎችም የሚያከብሩት ብሩህ ስዕል ለማሳየት፤” በማሰብ የቀረበ እንደሆነ ይገልፃሉ። በተጨማሪም፣ ደራሲው የምግባረ ሠናይነት ጉዳይ በማኅበራዊ መልኩ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ስለሆነ ለሰንበቴ፣ ለቆሎ ማኅበሮች እና ለመሳሰሉት መተው የለባቸውም፤ ሠፊ መዋቅር ተዘርግቶለት ከዛሬው በበለጠ ተግባራዊነት እንዲኖረው ለማሳሰብ፤” ስለፈለጉ መጽሐፉን መጻፋቸውን ይገልጻሉ።

በመጨረሻም፣ ከበድ ያለና ተገቢ ማሳሰቢያ ለአንባቢያኑ ያቀርባሉ። “ከክርስቲያን ተግባር ጋር ግንኙነት ያላቸው ትምህርታዊ ጽሑፎች ሌሎችንም ጉዳዮች ጨምረውና ደባልቀው ሲያቀረቡ ይገኛሉ። ሥነ ምግባር በጠቅላላው፤ በተለይም የክርስቲያን ሥነ ምግባራወ አስተሳሰብ ራሱን የቻለ ልዩ የዕውቀት ክፍል ዲስፕሊን መሆኑ ታውቆ በሌሎች ዘንድ በሀገራችንም “ጉባኤያት” ለሚባሉት እንደሚነገረው ተጠሪ ሊቅ፣ ማእምር ተመድቦለት በምርምር እና በንጽጽር ዘዴ ተጣርቶ የተቀናበረ ሥርዓተ-ትምህርት ሲስተም እንዲሰናዳ ያስፈልጋል፤” በማለት የጽሑፋቸውን ማእከላዊ ነጥብ ያቀርባሉ።

ለመጽሐፋቸው ዋና መነሻ የሆኗቸውን ሃሳቦች ያገኙት ከአባታቸው ከመምህር ገብረ ዮሐንስ ተሰማ ምግባረ ሠናይነት እና በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ ውስጥ ከሚታወቀው “አንቀጸ ብፁዓን” መጽሐፍ ንባብ እና ትርጓሜው ውስጥ የኢትዮጵያ ሊቃውንት እናዳቆዩት ከሚለው ነው። እዚህም እዚያም ተሰባጥረው የሚገኙትን የግዕዝ ሥነ-ጽሑፍ ነጥቦች “ምግባረ ሠናይ” ባሉት ሥነ-ባሕሪ አደላዳይ “ሕገ ልቡና”፣ በፈርጅ-በፈርጁ ሊደለድሉት/ሊያደራጁት ጥረት አድርገዋል። ሙከራቸውም ፈሩን ያለቀቀ ነበር። ... በአስተሳሰባቸውና በአቀራረባቸውም የገለልተኛነት ስፍራን ለመውሰድ ጥረዋል። የአንድ ፍልስፍና ትምህርት ቤት ጥገኛ ለመሆን አልፈለጉም። ከዚህም ከዚያም ጠቃሚ የሆኑትን ሃሳቦችና ነጥቦች ተፈላልገው በማጠናቀር፣ በቀጭኑ የሃሳብ ገመድ ላይ እንደሰርከስ ተጫዋች በብልሃት ለመጓዝ ተፍጨርጭረዋል። ይሁንና፣ ምንም እንኳን የገለልተኛነት መንገድን ለመውሰድ የሞከሩ ቢሆንም፣ የአንድ ትምህርት ቤት ተከታይ ከመሆን አላመለጡም። “ቃለ ሕይወት ፍኖተ ሕይወት” የሚለው ምዕራፍ፣ የደራሲውን የሃሳብ አካሄድና የአስተሳሰብ ፈለግ በይበልጥ የሚመሰክር ነው።

በተለይም፣ በግዕዝ ሥነ-ጽሑፋችን ውስጥ እዚያና እዚህ የተሰራጩትን ድንቅ ሃሳቦች አደራጅተውና አስፋፍተው በመፃፍ አንድ ጉልህ ፈር ቀደዋል። የሥነ ምግባርና የክርስቲያናዊ አርዓያነትን የአስተሳሰብ ጅረቶች እንዴት ለማገናኘት እንደሚቻል አውጠንጥነው ሲያበቁ፣ የኢትዮጵያውያንን የባህል፣ ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ሁለንተና “የሚያሻሽል ምግባረ ሠናይነት” እንዴት ሊገኝ ይችላል ሲሉ በጥልቅ መርምረዋል። የሚቻልበትንም መላና ዘዴ ገልጠዋል። ተፈላጊውም ሥነ ምግባር፣ ለሃገሪቱና ለህዝቧ በእጅጉ አስፈላጊና ዘላቂም ሊሆን እንደሚገባው አትተዋል።

ዶ/ር እጓለ፣ የሥነ ምግባር ትርጓሜን “ዘይቤ”ን እና ዓላማውንም አስመልክተው ሲገልጹ፣ “ቆስቋሽ ይፈልጋል የሰው ልጅ እንደሳት” ይሉናል። “ከክርስቶስ በፊት የነበረው ክርስቲያን” ያሉትን ሶክራቲስን ጠቅሰው፣ “በባህያችን ውስጥ በአምሳለ ዘር የተቀመጡ ጥንተ ነገሮች አሉ። እነሱን ፈልጎ ማግኘትና ማዳበር የምግባርና የሥነ ምግባር መሠረት ብቻ ሳይሆን፣ የትምህርትና የዕውቀት ጥረትም መድረሻው ነው። ይህም ከሌለ፣ እንደ ዕውር በዳበሳ መጓዝ ይሆናል፤” ማለቱን ያትታሉ ገጽ፣ 65-66። የሰውን የሕሊና ፍርዶች ለመቀስቀስና ለማንቃት ሲሉም የሕሊናዊነትንና የርሱንም ሥርዓት ከነአሠራር ባሕሪያቱ በመከተል ይቆሰቁሱታል። ከመነሾው የኢማኑኤል ካንትን አነጋገር፣ ማለትም “የሰው ትዝብት ያለ ሕልዮት ዕውር ነው። ሕልዮትም ያለ ትዝብት ዕውር ነው።” የሚለውን ማዕከላዊ ጉዳይ ያነሳሉ። ይህንንም የነገረ ዕውቀት አስተሳሰብ ወደ ሥነ ምግባር መስክ በመውሰድም፣ አንደኛ፣ ሕሊናዊነት በረቂቅ መልኩ ቅድሚያ ያለው መሆኑን ካስረዱ በኋላ፣ ሕሊናዊነት ከትዝብትና ከሕይወት ጋር ወዲያውኑ የሚተያይ የሚያገናዝብም መሆኑን ያስረዳሉ። በተቃርኖውም ሲያስቀምጡት፣ የሰው ሕሊና ያልተጻፈበት ባዶ ብራና tabula rasa አለመሆኑን ያትታሉ። ስለዚህም፣ የሰው ሕሊና ከሰው ትዝብትና ከሕይወቱ ጋር የሚተያይ ወደራዊነት parallelism ያለው መሆኑን ያሰምሩበታል ገጽ፣ 58።

በተጨማረም የካንትን ሃይለ-ሃሳብ ጠቅሰው፣ “ሠናይ ሥነ ምግባር ከቅድስናና ከመለኮት ባሕሪም ጋር ይዛመዳል። ከተራ ነገር የመጣ አይደለም። የስነ ምግባር ዋጋ የፈጠራ ወይም የስምምነት ጉዳይ ሳይሆን፣ ከሰብአዊነት ጋር ተናባቢ መሆኑንና ያኔ ሰውነት ገና ሲጀመር አንስቶም አብረው እንደነበሩ” በዝርዝር ያወሳሉ። ገጽ፣ 60 በሌላ በኩል፣ የነቢያትንና የሐዋርያትን የሥነ ምግባር መደልው አንስተው፣ በሃይማኖት ዓይን ሰው ሦስት የሥነ ምግባር ግዴታዎች እንዳሉበት ፕሮፌሰር ሐረልሰንን ዋቢ አድርገው ይናገራሉ። አንደኛው ሰው ለእግዚአብሔር ይፈጽመው ዘንድ የሚገባው ግዴታ ሲሆን፤ ለጣቂውም ሰው ለብጤው ወይም ለሕብረተሰቡ ሊፈጽመው የሚገባው ግዴታ መሆኑን ያወሱናል። ሦስተኛውም ግዴታ፣ ሰው ለገዛ ራሱ ሊፈጽመው የሚገባው ግዴታዎች እንዳሉበት በሠፊው ይተነትናሉ ገጽ፣ 72።

ከዚህ ጋር በማያያዝም፣ ደራሲው ሃሳባቸው አስታራቂ ነው። ማለትም፣ ደራሲው “ሦስቱም ግዴታዎች አንድ ናቸው፤ አንዱም ሦስት ነው።” አንድም ሦስትም፣ ሦስትም አንድም ናቸው እንደማለት ነው። የሥነ ምግባር ስረ-መሰረቱ ሕሊና ውስጥ የተጠራቀሙትን ዕውቀቶች ማውጣት ነውና። ይህንንም ሥሉስ አሳብ በተግባር ለማዋል፣ ሕገ ልቡና፣ ብርሃነ ልቡናና የሕሊና ወቀሳም መዘንጋት እንደሌለበት ደራሲው በአጽንዖት ይመክራሉ ገጽ፣ 62-69። በዚህ ጉዳይ ላይም፣ “ሰው ሀብታም ሆነ ደሀ ልዩነቱ የሚታየው በዝቅተኛ የዕውቀት እና የእምነት ደረጃ እስካለ ድረስ ብቻ ነው። ወደ ላይ ከፍ ካሉ በኋላ ወደ ፍጹምነት ደረጃ ሲደርሱማ የሚያስቡለት የሚሰስቱለት ነገር አይሆንም። እዚህ ከፍታ ላይ ያለ ሰው ብዙ ቢኖረው አይተርፈውም። ስለሚያካፍል፤ ትንሽም ያለው አያንሰውም። ብዙ ስለማይፈልግ ነው። ወደዚህ ዓለም ይዞት የመጣው፣ ሲሔድም የሚያከትለው አንዳች ነገር አለመኖሩን ያውቃልና ነው” ገፅ፣ 90። “አንቀጸ ብፁዓን”፣ እንደ ንፁህ ውሃ እንደ መስታወት የሚያገለግል መሆኑን ያወሳሉ። ራስን ለማየትና ከጉድፉም ራስን ለማንጻት፣ ሲከፋም የቱን ያህል ሰውየው እሾካም ፍጥረት እንደሆነ ለመረዳት “አንቀጸ ብፁዓን” ማገልገሉን ጠቅሰው፣ በዚህ አስተሳሰብ ማንበቡ አዋጪ መሆኑን ያሰምሩበታል ገጽ፣ 92።

መጽሐፉ በጠቅላላ መልኩ፣ የረቀቀን አሳብና ፈላሰፋዊ በሆነ መልኩ መግለጥ መቻሉን እንገነዘባለን። እንደመሰለኝ ከሆነ፣ ደራሲው ባማርኛ ተመዛዛኝ ቃል ባጡ ቁጥር እጃቸውን ወደ ግዕዝ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ዘርግተዋል። ባዷቸውንም አለመመለሳቸው እሙን ነው። ቀዋሚ ሊሆኑ የሚችሉ አያሌ ቃላትን፤ ለምሳሌ፣ “ዘይቤ፣ ሕልዮት፣ መልዕልት፣ ሕየንት፣ ላዕላይ፣ ልቡና፣ አንቀጽ፣ አኃዝ፣ ብፁዓን፣ መስተዋድድ፣ መስተፋቅር፣ ምጽዋት፣ ጸሎት.....” ወዘተርፈን ከግዕዝ ወስደዋል። እነዚህም ቃላት የረቀቀ የፍልስፍና አሳብን ለመግለጥ ተስማሚ ናቸው። በዚህ አኳኋን ሁለት ተግባራትን ፈጽመዋል። አንደኛ፣ የባዕድ ቃላትን ከመዋስና በጉራማይሌ ቋንቋ ግራ ከመጋባት ያዳኑን ከመሆኑም በላይ፤ ሁለተኛ፣ “አማርኛ ፍልስፍናን ለመሸከም አቅመ-ቢስ ነው፣ ልፍስፍስ ነው” ምንትስ ለሚሉትም ኮራጆች “ጓዳችሁን ፈትሹ” የሚል ይፋ መልዕክት አስተላልፈዋል። በእጅጉ የሚያስመሰግናቸውንም፣ ይህንን የመሰለ የቀላዋጭነትና የጠበበ አስተያየት ፈጽሞ ማሰቀረት ባይችሉም ቅሉ፣ በዚህኛውም መጽሐፍ ውስጥ በላቀ ብቃትና ትጋት ለአማርኛ ቋንቋ ባለውለታነታቸውን ፈጽመዋል።

 “ስለ ክርስቲያን ሥነ ምግባር መሠረት”፣ በቃላት አሰካክና አደራደሩ ስርዓትን የተከተለ ነው። ቃላቱ፣ ለአጫፋሪነትና ለአዳማቂነት ፈፅሞ ልሰፈሩም። “መጀመሪያ ቃል ነበረ፣ ቃልም....” የፈላስፋው አድናቆቱን መግለጫና የተረዳውን መርሆ መተንተኛ ሆነ፣ ብንል ሃሳቡን ሳያጠቃልለው አይቀርም። “ብዕር ዘፈተነ ወዘወጠነ” የሚለው ብሂል/ ዘዬ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ቦታ የለውም። እያንዳነዱ ቃል ሁነኛ ሙያ ያለው ብቻ ሳይሆን በስተኋላው ጥልቅ ኃሳብንም የተሸከመም ነው። ብዕራቸው ግጥምንና ስድ ንባብንም የያዘ ስለሆነ፣ አንባቢው በሁለቱም ስልቶች በኩል፣ ደራሲው ያላቸውን ተሰጥዖ ያደንቃል። መጽሐፉ ኅብረ-ጠባይ ያለው ስለሆነ አንባቢያኑ በእጅጉ ይረካሉ።

የመጽሐፉ ከቀዳሚው/ከታላቅ ወንድሙ በተሻለ የሕትመትና የአርትኦት እንከኖቹን አሻሽሎ መጥቷል። ከ27 አመታት በፊት ደራሲው ራሳቸው የጻፉትን “መቅድም” ይዟል። በገጽ 16 መጨረሻ ላይ መቅድሙ በታኅሣሥ 1978 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ መጻፉን ይገልጻል። ከገጽ 17 እስከ 26 ድረስም የሚኮመኮም የደራሲውን ቀልብ የሚጠቁም “መግቢያ” አካቷል። ከገጽ 165 እሰከ 170 ድረስም፣ የደራሲው የቅርብ ጓደኛና ዘመነኛ የነበሩት ፕሮፌሰር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ፣ “የደራሲውን ሥራዎችና አጭር የሕይወት ታሪክ” ሃተታ በውብ ቋንቋ ከትበውታል። የዋቢ መጽሐፍት ዝርዝርና የመፍትሔ ሙዳየ ቃላት ዝርዝርም ከገጽ 158 እስከ 162 ድረስ ተካቷል። በተጨማሪም ሁለት የመምህር ገብረ ዮሐንስ ተሰማና ስምንት የዶ/ር እጓለ ፎቶግራፎች ቀዳማይና አባሪ ሆነው ታትመዋል። ይህም፣ አባትና ልጁን ገጽታ ሕዝብ እንዲያውቀው በማድረግ በኩል ፋይዳ አለው።

ከገፅ 175 እስከ 187 ድረስ “ወደፊት የሚታተሙ” ተብለው የደራሲው ሦስት የትርጉምና አንድ የወጥ ግጥም ስራዎች ዝርዝር እንደሚታተም በድጋሚ ቃል ሰጥተውናል። አሳታሚዋ ወ/ሮ እህትአፈራሁ ተስፋዬ የደራሲው ባለቤት ናቸው በ”ማስታወሻ” ጽሑቸው ላይ እንዳሉት ገጽ፣ - ከአርዕስት ገጹ ቀፅሎ-ቀጽሎ እንዳሉት፣ “ተወዳጅ ልጆቻቸው የውድ አባታቸውን ምኞት ለመፈጸም ዝግጁ ነን፤” ብለዋልና፣ መጽሐፍቱ እንደሚታተሙ እምነቴ የጸና ነው። ሆኖም፣ መጽሐፍቱ ወደፊት ካልታተሙ፣ ዶ/ር እጓለን ሳይሆን ወራሾቻቸውን “ትዝብት” ላይ ይጥላል። ለማንኛውም እግዚአብሔር እንዲረዳቸው እመኛለሁ። እኛም አንባቢያን፣ ሌሎቹን የደራሲውን ስራዎች ከግማሽ ምዕተ-ዓመት በኋላ ለማንበብ ያብቃን።

ማጠቃለያ፤
መጽሐፉ እንደልብ ገበያ ላይ አይገኝም ነበር። እኔም፣ ወደ አቶ ሔኖክ ተስፋዬ የዶ/ር እጓለ ባለቤት ወንድም ናቸው፣ ዘንድ ደውዬ ነበር ውሱን ቅጂዎችን ያገኘሁት። የመጽሐፉ ሁለት ሺ 2,000 ኮፒ ለቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ደብር እድሳት እንዲረዳ አበርክተውታል። ይኸውም የሆነው፣ በዚህ ደብር መምህር ገብረ ዮሐንስ ከመላ ቤተሰባቸው ጋር ዕድሜ ልካቸውን ለረጅም ዘመን ሲያገለግሉ የኖሩ በመሆናቸው ነው። በተጨማሪም፣ ዶ/ር እጓለና የአባታቸውም መካነ መቃብር የሚገኘው በቀራንዮ መድኃኒዓለም በመሆኑ በርካታ ኮፒዎችም ለዚሁ ቤተ ክርስቲያን በነፃ ተሰጥተዋል። በመሆኑም፣ አከፋፋዮችና አንባቢያን መጽሐፉን ከሁለቱ ደብሮች ገዝተው የተለመደ የግብረ ሠናይ/ የሥነ ምግባር ዝንባሌያቸውን እንደሚያከናውኑ እምነቴ ነው።

መጽሐፉን በማሳተሙ በኩል የጣሩትን የዶ/ር እጓለ ገብረ ዮሐንስን ባለቤትና የማሳተሚያ ወጪውን የሸፈኑትን ልጆቻቸውን በሙሉ ከልብ እናመሰግናለን፣ እንዲሁም፣ የደራሲውን ጓደኛ ዶ/ር አባ ምክረሥላሴን በኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፣ የረጅም ጊዜ ሊቅ ባልደረባ ናቸው፣ መጽሐፉን በአርትኦትና በለቀማ ስራ ስላገዙ፣ በአንባቢያኑ ስም “ክብረት ይስጥልን!” ልላቸው እመዳለሁ።

ቸር እሰንብት!
ሰሎሞን ተሰማ ጂ.




semnaworeq.blogspot
 
ይህን ጽሁፍ ወዳጆችዎ ፌስቡክ ገጽዎ ላይ ለማስነበብ:  
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethioreaders.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
tizazu abebe [2501 days ago.]
 wow yamral

tizazu abebe [2501 days ago.]
 wow yamral

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
 
 
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
*
   
 
     
     
ፊደልን ከkeyboard ማመሳሰያ።
 

መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው© 2007 ዓ.ም ethioreaders.com