ደራሲያን በፊደል ማውጫ
   
 
 
ዶ/ር ሥርግው ሀብለሥላሴ
[1921 - 1995]
የደራሲው ሥራዎች
1.   ዳግማዊ ምኒልክ : የዐዲሱ ሥልጣኔ መሥራች(ታሪክ)
2.   ሓዋርያው ጳውሎስ በግሪክ ሀገር(መልክ፥ ገድልና:ነገረ:መለኮት)
3.   Ancient and Medieval Ethiopian History to 1270(ታሪክ)

ስለደራሲው በጥቂቱ

ዶ/ር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ
ሰኔ ፰ ቀን ፲፱፻፳፩ - ታህሣሥ ፳፱ ቀን ፲፱፻፺፭

ዶ/ር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ ከአባታቸው ከመሪጌታ ሐብለ ሥላሴ ዘውዴና ከእናታቸው ከወ/ሮ ዘውዲቱ ደስታ ሰኔ ፰ ቀን ፲፱፻፳፩ ዓ. ም. አዲስ አበባ ከተማ ተወለዱ። ባገራችን ሥርአትና ባህል መሰረትም እድሜአቸው ለቀለም ትምህርት በደረሰ ጊዜ አዲስ አበባ በሚገኘው የልደታ ደብር ፊደል ቆጥረው ዳዊት ደግመዋል። ከዚያም በኋላ ዘመናዊ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አዲስ አበባ የቅድስት ሥላሴ ትምህርት ቤት አጠናቀቁ። በጊዜው ተመርጠው ከቀረቡት የኢትዮጵያ ተማሪዎች አንዱ ሆነው ግሪክ አገር ቆሮንጦስ ከተማ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እዚያ ከሚገኘው መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ፲፱፻፵፩ ዓ. ም. ተላኩ። ይህንን ትምህርት አጠናቅቀው እዚያው ግሪክ አገር ባለው አቴና ዩኒቨርስቲ ገብተው ከአራት ዓመት በኋላ የባችለር ዲግሪያቸውን በቲዎሎጂ ጥናት ተቀበሉ። ከፍተኛ ትምህርታቸውን በመቀጠል ፲፱፻፶ እስከ ፲፱፻፶፪ ዓ. ም. ድረስ በጀርመን አገር በሚገኘው ቦን ዩኒቨርስቲ በጥንታዊ ታሪክ ምርምር የዶክትሬታቸውን ማእረግ ተቀበሉ። ከዚያም በኋላ አገራቸውን ለማገልገል ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ።

ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እስከ ፲፱፻፸ ዓ. ም. ድረስ ለ፲፯ ዓመታት በጊዜው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ የዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጥንታዊና መካከለኛ ዘመን ስልጣኔና ታሪክ የመጀመሪያ ምሁር ሆነው ሠርተዋል። በተጨማሪም ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የቲዎሎጂ አስተማሪ በመሆን አገልግለዋል። አገልግሎታቸውን በመምህርነት ብቻ ሳይወሰኑ ተመራማሪነታቸውንም አጣምሮ በተመለከተ እንደ London University ፤ በአሜሪካንም አገር እንደ Harvard University እና Princeton Univeristy ፤ በጀርመን አገር Heidlberg University፤ እንዲሁም በሆላንድ Lieden University በመሳሰሉት በዓለም በታወቁ ዩኒቨርስቲዎች በፌሎሽፕ እየተመረጡ በተለያየ ጊዜያት በከፍተኛ ደረጃ ልዩልዩ ጥናቶችን አከናውነዋል።

ዶ/ር ሥርግው በትምህርት ዓለም ካሳለፏቸው ዘመናት በላይ በመምህርነትና በምርምር እስከ ሕይወታቸው ፍጳሜ ድረስም ሠርተዋል። በዚህም መሠረት ለተማሪዎችና ለተመራማሪዎች እጅግ ጠቃሚ ሆነው የሚገኙ መጻሕፍትንና ስነጽሁፎችን አዘጋጅተው አሳትመዋል። ከድርሰቶቻቸው ውስጥ ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ብቻ ያህል፦

• በእንግሊዘኛ ቋንቋ ፲፱፻፷፩ ዓ. ም. የታተመው Bibliography of Ancient and Medieval Ethiopian History
• ፲፱፻፷፫ ዓ. ም. የታተመው Ancient and Medieval Ethiopian History to 1270

የተባሉት ይገኙበታል። እነኚህ ሁለት መጻሕፍቶች ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በአውሮፓና በአሜሪካ የሚገኙ እውቅ በሚባሉ ዩኒቨርስቲዎችና መጻሕፍት ቤቶች ቀርበው የኢትዮጵያን ታሪክ ለሚያጠኑ ሁሉ እንደ ዋና የምርምር ዶክሜንት reference document ሆነው እስከ ዛሬ ድረስ ይገኛሉ፤ ወደፊትም ማገልገላቸውን ይቀጥላሉ። እነዚህም መጻሕፍት ከታተሙ በኋላ ዶ/ር ሥርግው የፕሮፌሰርነት ማእረግን ለመሸለም በቅተዋል።

ዶ/ር ሥርግው በአማርኛ ቋንቋ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረበውን በ፲፬ ቅጽ የተተነተነውን ሰፊ የIትዮጵያ Oርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን መዝገበ ቃላት በአቀናባሪነት ያዘጋጁ ናቸው። ይህም ሥነጽሁፍ እስከ ዛሬ ድረስ ለቤተ ክህነት ሊቃውንት ተማሪዎችና ትልቅ አገልግሎትን በማበርከት ላይ ይገኛል። ከላይ ከተጠቀሱትም መጻሕፍት በተጨማሪ የኢትዮጵያን ጥንታዊ የሥነጽሁፍ አቀራረጽንና የመጻሕፍት አጠራረዝን የሚገልጽ Bookmaking in Ethiopia የተባለ መጽሐፍ አዘጋጅተው አቅርበዋል። በመጨረሻም በ፲፱፻፺፪ ዓ. ም. የአፄ ምንሊክን የሕይወት ታሪክ በተለይ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከውጪው ዓለም ጋር ኢትዮጵያን እንዴት እንዳገናኝዋት የሚያብራራ ብዙ ኢትዮጵያውን ያደነቁትን ድርሰትም አበርክተዋል። ከነዚህ መጻሕፍት በተጨማሪ ከሃያ ያላነሱ የኢትዮጵያንና የቤተ ክርስቲያንን ጥንታዊ ታሪክ የሚመለከቱ ልዩ ልዩ ሠፊ ስነጽሁፎች በበርካታ የዓለም ቋንቋዎች አዘጋጅተው አቅርበዋል።

በተጨማሪ ዶ/ር ሥርግው ለአገራቸው ካበረከቱአቸው ዋና ሥራዎች አንዱ ሆኖ የሚቆጠረው የIትዮጵያ ብራና መጻሕፍት ድርጅት መስራች ሆነው ያገለገሉበት ጊዜ ነበር። የዚህ ድርጅት የመጀመሪያ ሥራ አስኪያጅ ሆነው ከ፲፱፻፷፮ እስክ ፲፱፻፸፩ ዓ. ም. በተለያዩ ገዳማትና አድባራት በመዘዋወር በብዙ መቶ የሚቆጠሩ የጥንት ጽሑፎች በማይክሮፊልም ተቀርፀው ለታሪክና ለሚቀጥሉት ትውልድ እንዲቆዩ ያደረጉ ሰው ናቸው።

ከወይዘሮ ሰላማዊት መኰንን ጋር ሐምሌ ፲፱፻፶፰ ዓ. ም. በታእካ ነገስት በዓታ ቤተ ክርስቲያን የሠርግ ስነ ስርዓታቸውን ፈፀሙ። ከዚህም ትዳር አምስት ልጆች ናዖድ፣ ብሌን፣ ፈቃደ ሥላሴ፣ ናብሊስና እሜንን አፍርተዋል። ከነዚህም ልጆች መካከል የሦስቱን ትዳር ለማየት በቅተው፤ ሦስት የልጅ ልጆች ሆሣእና፣ ልያና እምነትን ለማቀፍ ችለዋል። ዶ/ር ሥርግው ባደረባቸው ሕመም ምክንያት ታህሣሥ ፳፱ ቀን ፲፱፻፺፭ ዓ. ም. በሚዩኒክ ከተማ በጀርመን አገር ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

ምንጭ: www.sergew.com
   
   
       
 
   
     
       

መጸሐፍ ለመዋዋስ መመዝግብ ያስፈልጎታል። ለመመዝገብ እዚህ ይጫኑ

ተመዝግበው ከሆነ እዘህ ይጫኑ
     
 

መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው© 2007 ዓ.ም ethioreaders.com