Warning: Undefined array key "access" in /home2/negadras/public_html/ethioreaders/articles/index.php on line 1
የልብ ወለድ ሥነጽሑፍ ጉዞ

ዋና ገጽ | ጦማር
+ - Font Size  
 
 

የልብ ወለድ ሥነጽሑፍ ጉዞ

  


ዮሐንስ አድማሱ
(መነን መጽሔት፤ግንቦት 1961 ዓ.ም )

አቅራቢ- ልሣነ ዮሐንስ
(የካቲት መጽሔት፤ሐምሌ-ነሐሴ 1980 ዓ.ም )

“ ፍጻሜ ለማድረስ የምሞክረው ተግባሬን በተጻፈው ኃይለ ቃል እንድታዳምጡ ፥ እንዲሰማችሁ፥ ከሁሉም ይልቅ እንድታዩ ማድረግ   ነው። ከሱ ወዲያ ሌላ ተግባር የለኝም። በሱም ውስጥ ሁሉም ነገር ይካተታል። ከተቃናልኝ በሚገባችሁ መጠን መበራታት ፥ መጽናናት ፥ፍርሀት ፥ ሞገስ የምትፈልጉትንም ሁሉ ታገኛላችሁ። ትሿት ዘንድ የምትገባችሁን --- ግና የዘነጋችኋትንም እውነት በጨረፍታ ታዩታላችሁ። ” ዮሴፍ ኮንራድ -ከ”ኒገር ኦፍ-ዘ ናርሲስስ” መቅድም

ሥነ ጽሑፍ የሰው ሐሳብና ስሜት በኪነት ኃይል ግዘፍ ነሥቶ አካል ገዝቶ የሚታይበት ጥበብ ነው። የአማናዊ ሥነጽሑፍም ምንጭ የሰው ልጅ ውነታ ሬያሊቲ ነው። እውነታውም በልደትና በሞት መካከል የተዘረጋው ህላዌ ነው።

 ሥነ ጽሑፍ ጠቅላላ ዓላማው ማስደሰት ነው። ይህንንም ጉልህ አላማ የሚፈጽመው  ሁሉን አቀፍ የሕይወት ኂስ  በማቅረብ ነው። ሥነ ጽሑፍ ጉልህ  ዓላማውን ለመፈጸም ጥራትና ወጥነት እንዲኖረው ያስፈልጋል።" በኑኀ ዘመን ፥ በቀን ብዛት የማይነቅዝና የማይሻግት" መሆን አለበት። አለበለዚያ አጉል ጒህና ወይም ብስና እንጂ ሥነ ጽሑፍ ሊሆን አይችልም። ሥነ ጽሑፍን ሥነ ጽሑፍ የሚያደርገው የደራሲው የኪነት ኃይል ፥ የማስተዋልና የማንጠር ችሎታ ፥ ያስተዋለውንና ያነጠረውን ከሰው ልጅ እውነታ ጋር በቋንቋ ኃይል አገናዝቦና አዋሕዶ "እነሆኝ !" ብሎ የሚያቀርብበት ልዩ ችሎታው ነው። ግልብ ደራሲ ግልብ ተመልካች ነው። ጽሑፉም በዚያው ልክ ግልብ ይችርቻሮ ጽሑፍ ይሆናል።

ይህን አባባል መሠረት በማድረግ  ከ1933 እስከ 1960 ድረስ ስላለው የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ጉዞ አንዳንድ ነነር ለማውሳት እወዳለሁ።

በጠቅላላው በነዚህ በሀያ ሰባት ዓመታት  ውስጥ አማርኛ ያፈራው ሥነ ጽሑፍ ብዛት እንጂ ጥራት የለውም። ከጥልቀት ይልቅ ግልብነት፥ ከውበት ይልቅ አስቀያሚነት አስቀያሚነት ውበት ነው ወይም ውበት አለው ካልተባለ በቀር፥ ከሥነ ጽሑፋዊ ዕውነት ይልቅ የአንቀፀ ብጹዓን ምኞት ይገኝበታል። ሥነጽሑፍ የሕይወት ኂስ በመሆን ፈንታ የወሸነኔ ስሜት መግለጫ ሆኗል። እስካሁን ድረስ አካሄዱ አጉል ነው፤ የጎድን ነው። አቅጣጫ ያለው አይመስልም። የወደፊት አካሄዱን መተንበይ ባይቻልም እስካሁን ድረስ ተመልክተን በተገነዘብነው አካሄድ ለወደፊት አካሄድ አብነት የሚሆን አይደለም። በአጭሩ በሀያሰባት ዓመታት ዕድሜ ውስጥ ያፈራነው  የአማርኛ ሥነጽሑፍ ከአዝመራው ጋር ሲነፃፀር ደረጃው፥ ጥራቱና አስደሳችነቱ አለመጠን ዝቅ ያለ ነው። እያደር ይጫጫል ፤ እየሰነበተ ይደገድጋል ፤ እየባጀም ፥ እየከረመም ይመነምናል። ለዚህ አሳዛኝ፥ ከቶም ድቀታዊ ሁነት ምክንያት ከሆኑት ከብዙዎቹ ነገሮች ሦስቱን ወቅሼ ከመዘርዘሬ አስቀድሜ ጥራት ፥ ወጥነት፥ ጥልቀትና ውበት ያላቸው ሁለት መጻሕፍት መጥቀስ እወዳለሁ

ሁለቱ መጻሕፍት "እንደወጣች ቀረች"ና "ፍቅር እስከ መቃብር" ናቸው። ከነዚህ ከሁለቱ ደረጃ ባይደርሱም ሌሎች መጻሕፍት በመጠኑ አሉ።

እንዚህ ሁለት መጻሕፍት የኪነት ውጤቶች ናቸው። ጥልቀታቸውም ፥ ውበታቸውም፥ ሌላውም መልካም የምንለው ጥራታቸውም ከዚሁ ከኪነት መንፈሳቸው ይሠርፃል። በ"ቴክኒክ" (ቅርጽ)

ከሞላ ጎደል ምሉዕ ናቸው። በትልም ፥ በባሕርያት፥ አቀራረብ፥በአተራረክ፥በቋንቋ ወዘተ እነዚህ ሁለት ልብወለድ መጻሕፍት በመጀመሪያው አንቀጾች የሰነዘርኳቸውን ሐሳቦች በሙሉም ባይሆን በከፊል አቀናብረው ይዘዋል። 

ሁለቱም ሁለት ልዩ እውነታ ያቀርባሉ ፤ በአንድ ነገር ይተባበራሉ ፤ ይገናኛሉ። ሁለቱም ያቀረቡልን የሕይወት ኂስ ነው። ሁለቱም በየገጾቻቸው በሚገኙት ቃላት ኃይል እንድናደምጥ፥እንዲሰማን፥ በተለይም እንድናይ ለማድረግ ሞክረዋል።  ይኸው ሙከራቸው በሙሉም ባይሆን በከፊል ስለተቃናላቸው የምንፈልገውን ነገር እንድናገኝ አድርገዋል። ለዚህም እኛ አንባቢያን ሐሴት እናደርጋለን።በጠቅላላው ከ1933 ዓ.ም ወዲህ ጥሩ የምንላቸው አማርኛ (የኪነት) መጻሕፍት ጥቂት ናቸው ።ከመቶ ዘጠና ዘጠኙ "ብላሽ" ናቸው። ለምን ?

ደራስያኑ በደፈናው ወይም በጠቅላላው ስለ ልዩ ልዩ የኪነት ጽሑፍ ቴክኒክ አያውቁም። ቢያውቁም አይጨነቁም። ጽሑፋቸውን የቴክኒክ ግብዝነት አለልክ ያጠቃዋል። የጽሑፍ ቴክኒክ ለኪነት ጽሑፍ ዓቢይ ከሆኑት ነሮች አንዱና  ዓይነተኛው ነው። የሀገራችን የኖረ  የቆየ የጽሑፍ ቴክኒክ አለ፥ የውጭ ሀገርም የጽሑፍ ቴክኒክ አለ።፥ ደራሲያኑ የውጪውንም ሆነ የሃገራችንን የጽሑፍ ቴክኒክ አብስለውና ጠንቅቀው አያውቁም። 

በሀገራችን ለምሳሌ የታወቀ ፥የተለመደ ፥ከሙያ የዋለ የገድል አጻጻፍ ቴክኒክ አለ። ገድል የአንድ ሰማዕት ወይም የአንድ ጻድቅ የሕይወት ታሪክ ነው። ገድል በጠቅላላው የሚያወጋው ወይንም የሚተርከው የሰማዕቱን ወይንም የጻድቁን ተጋድሎ ነው---ስለሰማያዊ ልዕልና ፥ ለሰማያዊ ክብር፥ መንፈሳዊ የሆነ ምድራዊ ተጋድሎ። አተራረኩ በመንፈሳዊ እውነታ ላይ የተመሠረተ ነው። ትልምና ባሕርያት፥ የአተራረክ ስልትም አለው። የአተራረክ ፈሊጥም አለው። ብሎም "ገድለ ተክለ ሃይማኖትን" መጥቀስ ይበቃል። አንቱ የሚባል ወይም ለመባል የሚሻ ደራሲ የገድልን አጻጻፍ አጥርቶ ማወቅ ግዴታው ነው። ብዙ ነገር ይማራል። አያሌ ጥበብን ይቀስማል። በቴክኒኩም ይበለጽጋል። 

የቅኔም ቴክኒክ አለ። ይኽንንም ቴክኒክ ማወቅ የማንኛውም ደራሲ፥ በተለይም ገጣሚ ተግባርና ግዴታ ነው። (የቀረውን እንዳለፈው ያነቧል።


ሌሎችም ብዙ የጽሑፍ ቴክኒኮች በሀገራችን በብዛት ይገኛሉ። የተረት፣የሙሾ፣የእንቆቅልሽ፣ የእንካ ስላንቲያ፣ የቀረርቶ ወዘተ። እነዚህን ሁሉ አንቱ የሚባል ወይል ለመባል የሚሻ ደራሲ አጠናቆ ማወቅ ግዴታው ነው።

ከውጪውም ዓለም የተገኙ የጽሑፍ ቴክኒኮች አሉ። የተውኔት ፣የረጅም ልብወለድ ወዘተ። ደራስያናችን (ከ1933 -1960 የነበሩትን ማለቱ እንደሆነ አንዘንጋ) የውጪውንም የጽሑፍ ቴክኒክ አጥርተው አያውቁትም። በአጭሩ የሚጽፉት አገኝ አጣቸውን ነው። የሚጽፉት በንዝህላልነት፥ ብዙ ጊዜም በግዴለሽነት፥ በማንአለብኝ መንፈስ ነው። ለዚህም ምስክር የሚሆኑ ብዙ መጻሕፍት አሉ። ለጊዜው ግን አንዱን መመልከት ይበቃል። "አድልዎን በሰይፍ" መጽሐፉ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው "ብላሽ ነው" ፤ ጉድለቱ ወሰን፥ዱካ የለውም። ጥራቱ ጉድለቱን ጉልህ አድርጎ ማሳየቱ ነው። ታሪኩ የሚተርከው በአንደኛው መደብ፥ ነጠላ ቁጥር እኔ ነው። አንድ ታሪክ በአንደኛ መደብ መተረክ የተለመደ ነው። ይሁን እንጂ ታላቅ ጥንቃቄ ይጠይቃል። አደገኛ ነው። በተለይም ለጀማሪ ደራሲ ክፉ ፥ አዚመኛ ፥ አንጋዳ ነው።

የተጠቀሰው መጽሐፍ ታሪኩን እስከመጨረሻው ድረስ በአንደኛ መደብ ይተርክና መጽሐፉ ሊያበቃ ጥቂት ሲቀረው "ሞትኩ" ያላል። ይኽን የሚለው የታሪኩ ዋና ባሕርይ ነው። ባሕርዩ መደቡ አንደኛ መደብ ነው። "ሞትኩ" ካለም በኋላ ታሪኩን ይተርካል። ሙቷል ፥ በአጸደ ሥጋ አይገኝም ማለት ነው። ይኽ ንስሐ የሌለው የቴክኒክ በደል ነው። እንዲህ ያለው በደል የሚፈጸመው ምናልባት ካለማወቅ ይሆናል፤ ምናልባትም ከንዝህላልነት ፥ ወይም ከንቀት ፥ ምክንያቱ የቱ እንደሆነ አላውቅም። ከደራሲው ጋር መነጋገር ምክንያቱን ለማወቅ ይረዳ ይሆናል። ይኽንንና ይኽን የመሰሉ የቴክኒክ ጉድለት ያለባቸው መጻሕፍት እጅግ ብዙ ናቸው።

የሚከተሉትን ይመለከቷል "ውብ ነበረች"፥ "ሥራ ገንዘብና ጓደኛው" ፥ "የጉድጓዱ ምሥጢር" ፥ "ንስሐ" ፥ "እውነት ስትጠፋ" ፥ "የሐሳብ እስረኛ" ፥ "ከማን አንሼ እኛም ይድረሰን" ፥ ..." እነዚህ መጠቀስ ከሚገባቸው በጣም ጥቂቱ ናቸው።


የዘመናችን ደራሲያን (ከ1933—1960 የነበሩት) በጽሑፍ ቴክኒክ በኩል ከሃገራቸውም አልሆኑ ከውጪውም አልሆኑ። የሃገራችንንና የውጪውን አቀላቅለውም መጢቃ ቴክኒክ አላቀረቡልንም። ወይም ከሁለት አንዱን ብቻ ተከትለው ወጥ ጽሑፍ አላበረከቱም እስከአሁን (ከ1933 --- 1960) ድረስ ቴክኒካቸው ውጥንቅጥ ፥ የልብ ትኩሳት የልብ ቃር የሚሆን አጉል ቅይጥ ነው -ከሥርዓት ይልቅ ምስቅልቅል የሰፋነበት ነው።

ምናልባት ከዚህ ውጥንቅጥ ፥ ከዚህ ምስቅልቅል ኢትዮጵያዊ የሆነ ወጥ ቴክኒክ እንደ ብሂል ፥ እንደ ሠረዝ  ፥ እንደጎዳና ቅኔ ፥ ... ያለ ይጸነስ ይሆናል ይኽ መቸም ምኞት ነው። ምኞቱ እውነት እንዲሆን የእኔ ብቻ ሳይሆን ለአማርኛ ሥነጽሑፍ ማደግ ፥ መዳበርና ኃያል መሆን የሚቆረቆር ኢትዮጵያዊ ሁሉ ፍላጎት ነው።

ሁለተኛው ነቁጥ፥ የኂስ ጥበብ አለመለመድና የኀያሲ አለመኖር ነው። በባሕላችን የኂስ ጥበብ አልነበረም፥ የሚሉ ብዙ ሰዎች አሉ። ከዚህም የተነሳ ደራሲያኑ መጻሕፍታቸው በጋዜጣም ሆነ በመጽሔት ሲተቹ (በቀጥተኛ ኂስ) አንዳንዶቹ ያኮርፋሉ። አንዳንዶቹ ይዝታሉ ፥ አንዳንዶቹ በጋዜጣም ሆነ በመጽሔት ይሳደባሉ። ይኽ መንፈስ ከየት እንደመጣ አላውቅም። ጉዳዩ ጥልቅ ምርምርና ጥናት የሚያስፈልገው ነው።

ይሁን እንጂ አንድ የማውቀው ነር አለ። ኂስ በቅኔ ቤት የተለመደ ነው። የቅኔ ተማሪ ፥ከቅኔ ትምህርት ሌላ፥ በጥበቡ የሚጎለምሰው ፥ የኪነት ተውህቦውን የሚያተባው ፥ የሚያራቅቀውና የሚያደራጀው በኂስ ጥበቡ ነው። የተማረውን ቅኔ የቀለም ጓደኞቹና መምህሩ ይተቻሉ። እሱም እንደዚህ ያደርጋል። ተማሪዎቹ የመምህራቸውን ቅኔ ይተቻሉ፥ አንዳንዴም  ብትንትኑን ያወጡታል። ኩርፊያና ስድብ ፥ ዛቻና ቅያሜ የለም ፥ ይህ መልካም ጥበብ እያለ ደራስያናችን ለምን በኂስ (በደንበኛ ኂስ)  ይቆጣሉ?

ኂስ ለሥነ ጽሑፍ ሕይወት መጠበቂያ ዓይነተኛውና ፍቱን መድኃኒቱ ነው። ኂስ ጉድለትንም ጥራትንም መግለጫ ጥበብ ነው። ማስተማርያም ነው። እንደ ስድብ፥ እንደ ነውር መቆጠር የለበትም። በኂስ መስተዋትነት ስሀውን የማይከላ ሥነ ጽሑፍ ሆነ ደራሲ ከበድን አንድ ነው። ተገቢ ቦታውም ቤተ መዘክር ነው።

ሦስተኛው ነቁጥ  (ከ1933—1960)  ያለፉት የሀያ ሰባት ዓመታት የአማርኛ ሥነጽሑፍ ሦስተኛ ጉድለት የቋንቋው ነው። በጠቅላላው ቋንቋው ውበት ፣ ጥራትና ተጠየቅ  የተለየው ፥ በጸያፍ (ሰዋስው) የተበከለ ፥ በቃላት እጥረት የተሞሸረ ነው። ይኽን ጉድለት የፈጠሩ ደራስያን ናቸው እንጂ ቋንቋው አይደለም። ቋንቋው ማለፊያ ባለሙያ ልባም ደራሲ ካገኘ ብዙ ስንፍና የሚያስገባ አይመስለኝም። 

ለዚህም አብነት የሚሆኑ የሚከተሉት ቀደምት ደራስያን ናቸው።አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ወልደ አባ ተክሌ  ፥አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ፥ ዮፍታሔ ንጉሤ፥ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ፥ አለቃ ታዬ ፥  ወዘተ….። 

በመጻሕፍት በኩል የተጠቀሱት ደራስያን ከጻፏቸው መጻሕፍት ሌላ መጽሐፈ መነኮሳትን፥ አርባዕቱ ወንጌልን መመልከት ይበቃል።

የአሁኑ ዘመን ደራሲያን(ከ1933—1960 የነበረው)  አማርኛ ለምን ተበላሸ? በዚሁስ የሚቀጥለው ለምንድር ነው? 

ሁለት ምክንያት መጥቀስ ይቻላል። ትምህርት ቤት በነበሩበት ጊዜ ጥሩ አማርኛ እንዲማሩ አልተደረገም። ሁለተኛ ደራስያኑ የሚያነቡ አይመስልም። በቋንቋቸው ጥራት ጥሩ የሆኑ፥  ተነበው በቋንቋቸው ጥራት፥ በዘይቤአቸው ውበት የሚለዩ መጻሕፍት ጠፍተው አይደለም፤  አሉ። ፈልጎ ማንበብ ብቻ ነው የሚያስፈልገው። መጻሕፍቱን የጠቀስኳቸው ስለ ይዘታቸው ሳይሆን  ይዘታቸውን የማይፈቅዱ ይኖሩ ይሆናል በጠቅላላው ስለቋንቋቸው ጥሩነት ነው፣ ስለምናባቸው (ኢማጂኔሽን) ስፋት ነው ፤  ስለዘይቤአቸውም አስገራሚነትና ውበት ነው። ዛሬ ያሉንም ሆኑ ወደፊት የሚነሡት ደራስያን እነ ዚህና እነዚህን ቢያነቡ ቋንቋቸው ይዳብራል። አስተሳሰባቸው ይተባል ፥ ሐሳባቸውን ፥ ጃ ሳይላቸው እንደልባቸው መግለጽ ይችላሉ። የማይሰለች ለዛና ወዝ፥ ውበትና ጥራት ያለው "ዞሌ" ጽሑፍ መጻፍ ይችላሉ።

የጽሑፌ ሐይለ ቃል በድርሞ መልክ የሚከተለው ነው፦

ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት (ከ1933-1960 ዓ.ም) ውስጥ ያፈራነው የአማርኛ ሥነጽሑፍ በጠቅላላው ጥራቱንና ወጥነቱ አለመጠን ዝቅ ያለ ነው። ይኽም የሆነበት ምክንያት ሀ/በቴክኒክ ጉድለት ፤ ለ/በሂስና በሃያሲ እጥረት፤ ሐ/በደራስያኑ አማርኛ መበላሸት።

ከነዚህም ምክንያቶች ለ"ሀ"ና ለ"ሐ" ኃላፊዎቹ በከፊል ደራስያኑ ናቸው። አያነቡም። የማወቅና የማጥናት ጉጉት የላቸውም። ለሁለተኛው ምክንያት "ለ" ኃላፊነታቸው ኢርቱዕ ነው--ኂስ አለመቀበላቸው ወይንም በኂስ መበርገጋቸው።  የአማርኛ ሥነጽሑፍ የተሻለ ደረጃ እንዲይዝ ፥ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ተፅኖው ለመላው ዓለም እንዲተርፍ ከተፈለገ ደራሲያናችን ዛሬ ያሉትም ሆኑ ወዲፊትም የሚነሱት ረዥም ተጋድሎ ማድረግ አለባቸው። የታጋድሎው ጐዳና ረዠም ሆኖ ጉዳጉድ የበዛበት ፥ ቅርቅፍት ነው። ተስፋ መቁረጥ ግን አያስፈልግም። እንደ ጥንታውያኑ ለሀገራቸው ነፃነት ሕይወታቸውን ፥ በየጎራው ፥  በየሜዳው ፥ በየአረሁ እንደተሰውት ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን ባጭር ታጥቆ ፥የሥነጽሑፍ ዘገር ነቅንቆ የሥነ ጽሑፍ ጋሻ መክቶ
-ለሥነ ጽሑፍ መጋደል፥ የያንዳንዱ ደራሲ ፈንታ ነው።

[ኢትዮጵያውያን ደራስያን በዓለም የሥነ ጽሑፍ ሸንጎ ላይ ተሠልፈው የሚወዳደሩበትን ዕለት በናፍቆት እጠባበቃለሁ። ዮሐንስ አድማሱን በ1967 ዓ.ም ሞት ባይቀድመው ኖሮ በናፍቆት ከጠበቀው ዛሬ (ከ1960- 1980) ስንቱ እጅ ተግባራዊ እንደሆነና ወይም እንዳልሆነ እሱው በበየነ ምንኛ ባማረ? ዳሩ ምን ያደርጋል? አልሆነለትምና “ተወርዋሪ ኮከብ “ሆነ - እሱ  ዮፍታሔ ንጉሤን ይለው እንደነበረ- ልሳነ ዮሐንስ ]



የካቲት መጽሔት
 
ይህን ጽሁፍ ወዳጆችዎ ፌስቡክ ገጽዎ ላይ ለማስነበብ:  
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethioreaders.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
asmelash teka [3409 days ago.]
 ስለ ስነፅሁፋዊ ኢልበወለድ ምንነት አንዳንድ ነገር ብትለኝ ምስጋናዬ ወሰን የለውም

ermias [3325 days ago.]
 Thank you ethioreaders for allowing us to read such scholarly reading about ethiopian litreature. I have learned a lot from this subtle piece I hope it awakens many writers to make corrections and take the right path.

mesfin [3324 days ago.]
 Good reading

nava [3322 days ago.]
 We need serious reading like this.

nebyou [3322 days ago.]
 Real Intellectual Piece.

Betty [3039 days ago.]
 የልብ ወለድ መፅሀፍትን ከማስነበብ ባለፈ ትርጉሙንም አያይዞ ማቅረብ ተመራጭ ነው እለሁ።

amanuel ashagrie [2918 days ago.]
 የኢትዮጵያን ለኢትዮጵያውያን

ketema koysha [2857 days ago.]
 ማንበብ የልብ ርካታ ይሰጣል!!

መሙለሉገጌ [2722 days ago.]
 ፌደዘዘአ

biruke tsegaw [2543 days ago.]
 its very good

Abdi [2502 days ago.]
 Very Good !!!

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
 
 
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
*
   
 
     
     
ፊደልን ከkeyboard ማመሳሰያ።
 

መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው© 2007 ዓ.ም ethioreaders.com